Ezra 5

ለዳርዮስ የተላከ የተንትናይ ደብዳቤ

1በዚያን ጊዜ ነቢዩ ሐጌና የአዶ ልጅ ነቢዩ ዘካርያስ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ አይሁድ ከእነርሱ በላይ በሆነው በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው። 2ከዚያም የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራት ተነሡ፤ የሚያግዟቸውም የእግዚአብሔር ነቢያት አብረዋቸው ነበሩ።

3በዚህ ጊዜ በኤፍራጥስ ማዶ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና ተባባሪዎቻቸው ሄደው፣ “ይህን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራትና ውቅሩንም ለመጠገን የፈቀደላችሁ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው። 4ደግሞም፣ “ይህን ሕንጻ የሚገነቡት ሰዎች ስም ማን ይባላል?” በማለት ጠየቋቸው
የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ይመ፤ የአረማይኩ ትርጕም እንዲህ ይላል፣ ይህን ሕንጻ የሚገነቡትን ሰዎች ስም ነገርናቸው
5የአምላካቸው ዐይን ግን በአይሁድ መሪዎች ላይ ነበረ፤ ነገሩ ወደ ዳርዮስ ደርሶ የጽሑፍ መልስ እስኪያገኙ ድረስ አልተከለከሉም።

6በኤፍራጥስ ማዶ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይ፣ ተባባሪዎቻቸውና በኤፍራጥስ ማዶ የነበሩ ሹማምት ለንጉሥ ዳርዮስ የላኩት ደብዳቤ ቅጅ ይህ ነው፤ 7የላኩትም ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፤

ለንጉሥ ዳርዮስ፣

የከበረ ሰላምታ እናቀርባለን።

8የታላቁ አምላክ ቤተ መቅደስ ወደሚገኝበት ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደን እንደ ነበር በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን በታላላቅ ድንጋዮች እየገነቡና ቅጥሩንም በወፍራም ምሰሶዎች እየሠሩ ነው፤ ሥራው በትጋት በመከናወንና በእነርሱም አመራር በመፋጠን ላይ ይገኛል።

9እኛም መሪዎቹን፣ “ይህን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራትና ይህንም ውቅር ለመጠገን የፈቀደላችሁ ማን ነው?” ብለን ጠየቅናቸው። 10የመሪዎቻቸውን ስም በጽሑፍ እናሳውቅህ ዘንድ ስማቸውን ደግሞ ጠየቅን።

11የሰጡን መልስ ይህ ነው፤

“እኛ የሰማይና የምድር አምላክ አገልጋዮች ነን፤ አሁንም እንደ ገና የምንሠራው ቤተ መቅደስ፣ ከብዙ ዘመናት በፊት ታላቁ የእስራኤል ንጉሥ ሠርቶ የጨረሰውን ነው።
12ነገር ግን አባቶቻችን የሰማይን አምላክ አስቈጥተውት ስለ ነበር፣ ለባቢሎኑ ንጉሥ ለከለዳዊው ናቡከደነፆር አሳልፎ ሰጣቸው፤ እርሱም ይህን ቤተ መቅደስ አፈራርሶ ሕዝቡን ወደ ባቢሎን አፈለሰ።

13“ይሁንና ቂሮስ፣ የባቢሎን ንጉሥ በሆነ በመጀመሪያው ዓመት ይህን የእግዚአብሔር ቤት እንደ ገና እንዲሠሩ ንጉሥ ቂሮስ ትእዛዝ ሰጠ። 14ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ አውጥቶ ባቢሎን በሚገኘው ቤተ መቅደስ
ወይም፣ ቤተ መንግሥት
ውስጥ ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች ከባቢሎን ቤተ መቅደስ አስመጣ። ከዚያም ንጉሥ ቂሮስ፣ አገረ ገዥ አድርጎ ለሾመውና ሰሳብሳር ተብሎ ለሚጠራው ሰው ሰጠው፤
15ቀጥሎም፣ ‘እነዚህን ዕቃዎች ይዘህ ሂድና በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ አኑራቸው፤ የእግዚአብሔር ቤት ቀድሞ በነበረበት ቦታ እንደ ገና ይሠራ’ አለው።

16“ስለዚህ ይህ ሰሳብሳር መጥቶ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሠረት ጣለ፤ ከዚያን ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እነሆ በመሠራት ላይ ነው፤ ሆኖም ገና አላለቀም።”

17አሁንም ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ቢሆን፣ ይህ የእግዚአብሔር ቤት በኢየሩሳሌም እንዲሠራ ንጉሥ ቂሮስ በርግጥ ትእዛዝ ሰጥቶ እንደ ሆነ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤት የተቀመጡት መዛግብት እንዲመረመሩ ያድርግ፤ ከዚያም ንጉሡ ስለዚህ ጕዳይ የወሰነውን ይላክልን።

Copyright information for AmhNASV